የደንብ መተላለፍን በመቀነስ የላቀ አፈፃፀም ያስ...

image description
- In code inforcement    0

የደንብ መተላለፍን በመቀነስ የላቀ አፈፃፀም ያስመዘገበው ክፍለ ከተማ ልምዱን አጋራ

የደንብ መተላለፍን በመቀነስ የላቀ አፈፃፀም ያስመዘገበው ክፍለ ከተማ ልምዱን አጋራ

              27/06/2017 ዓ.ም
             ****አዲስ አበባ****

ባለስልጣኑ በ2017 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ክፍለ ከተሞች 25% የደንብ ጥሰትን እንዲቀንሱ ያወረደውን መሪ እቅድ 50.4% በመቀነስ 100% አስመዝግቦ ውጤታማ የሆነው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት በዛሬው ዕለት ልምዱን ለሌሎች ክፍለ ከተሞች አጋርቷል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ የተመራው የልምድ ልውውጥ ልዑካን ቡድን የተቋሙን ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የማዕከል ዳይሬክተሮችና የ11ዱንም ክፍለ ከተማ   የደንብ ማስከበር  ጽ/ቤት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዳኜ ሂርጳሳ የልምድ ልውውጥ ልዑካን ቡድኑን የጽ/ቤታቸው፣የአመራራቸውና የሰራተኛው ቅንጅታዊ አሰራር ልምድና ተሞክሯቸውን በዝርዝር አስቃኝተዋል።

ስትራቴጂካዊ የሆነ የአመራር ስልትን በመንደፍ ከክፍለ ከተማ እስከ ወረዳ ድረስ ስራዎችን በቅንጅት መምራት በመቻሉ የደንብ ጥሰትን ከእቅዱ በላይ ለመቀነስ ማስቻሉን አቶ ዳኜ አስገንዝበዋል። 

በተለይ የቁጥጥርና ኢኒስፔክሽን፣ የቅድመ መከላከልና የግብረ-ኃይል ቡድኑ እስከ ወረዳ ድረስ ባደረገው ጥልቅ ድጋፍና ክትትል ዘጠኙንም የደንብ መተላለፎች ላይ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።

የተሰሩ ስራዎችንም የካይዘን ፍልስፍናን ተግባራዊ በማድረግ መረጃዎችን በማጥራት፣ ማደራጀት፣ ማንፃት፣ ማቀናጀትና ማዝለቅ የተቻለ መሆኑን በልምድ ልውውጡ ተመላክቷል።

የልምድ ልውውጡ ተሳታፊ አካላትም ክፍለ ከተማው በ2017 ግማሽ ዓመት ቀዳሚ እንዲሆን ያበቃውን አፈፃፀም በአካል ወርደን በማየታችን ውጤቱ የሚገባውና  እኛም በርካታ ልምዶችን የቀሰምንበት ነው በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ጽ/ቤቱ በሪፎርም ስራም በክፍለ ከተማው ካሉ 36 ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር ተወዳድሮ በአንደኛነት ማጠናቀቁ በእርግጥም ሌሎች ክፍለ ከተሞች ልምዱን በመቅሰም የተቋሙን ራዕይ እውን ለማድረግ የሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ ማሳያ መሆኑን የገለፁት የልምድ ልውውጥ ቡድኑን የመሩት የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ገልፀዋል።

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የተገኘውን ሁሉን አቀፍ የላቀ አፈፃፀም ጠምሮ በመቀመር ከማዕከል እስከ ወረዳ ብሎም ሌሎች የከተማ አስተዳደሩና የክልል ከተማ ተቋማት ጭምር እንዲጋሩት ማድረግ እንደሚገባ ዋና ስራ አስኪያጁ በአፅንኦት አስገንዝበዋል።

ዘገባው:- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ኮሙኔኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው።


Comments

Nothing was found.

Leave Your Comments