ባለስልጣኑ የከተማዋ ብክለትን በቅንጅት ለመከላከል የውይይት መድረክ አካሄደ
ባለስልጣኑ የከተማዋ ብክለትን በቅንጅት ለመከላከል የውይይት መድረክ አካሄደ
24/06/2018 ዓ.ም
**አዲስ አበባ**
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለስልጣን የአከባቢ ብክለትን በቅንጅት ለመከላከል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አከባቢ ጥበቃ ባለስልጣን፣ከጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ እና ከሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ጋር የጋራ የውይይት መድረክ አካሂዷል ።
በመድረኩ የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ የአከባቢ ብክለቶችን በዘላቂነት ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከርና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ላይ በትኩረት በመስራት ቆሻሻን የመፀየፍ ባህላችንን በማሳደግና አወጋገዳችንን በማዘመን ብክለትን በዘላቂነት መከላከል እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከቅጣትና ከደንብ ማስከበር ባለፈ፣ ህብረተሰቡ ስለ አካባቢ ጥበቃና ስለ ቆሻሻ ጉዳት በቂ ግንዛቤ አግኝቶ ቆሻሻን የሚፀየፍ ትውልድ እንዲፈጠር በትኩረት መስራት እንደሚገባና ህግንና ደንብን ተላልፈው አካባቢን በሚበክሉ አካላት ላይ ከደንብ ማስከበር ስራ እንደሚሰራና በሚተላለፉ አካላት ተጠያቂነት እንደሚሰፍን አስገንዝበዋል።
በመድረኩ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አከባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር እሸቱ ለማ የአከባቢ ጉዳይ ሁሉንም ህብረተሰብ የሚመለከት እንደመሆኑ ከተማችንን ንጹህ ውብ ለነዋሪዎቿ ምቹና ለቱሪስት መስብ የአፍሪካ ተምሳሌት እንድትሆን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራትና ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል ።
በንግግራቸው የአከባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የከተማውን ዘላቂ የአከባቢ እንዲሁም ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚደግፍ ንጹህ ፣ ጤንነቱ የተጠበቀ አከባቢን ለዜጎች ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።
በእለቱ የፕላስቲክ ከረጢት ከሚሰጠው ጥቅም ይልቅ በአከባቢው የሚያሳድረው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን በጥናት ተረጋግጦ ፕላስቲክ ከረጢት ከገበያ እንዲወጣና አገልግሎት ላይ እንዳይውል መደረጉና ቅጣት እንደሚኖረው ማህበረሰቡ ተገንዝቦ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ በመድረኩ ተገልጿል ።
የአከባቢ ብክለትን በቅንጅት ለመከላከል የሚያግዝ የውይይት መነሻ ሰነድ በአከባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የብክለት ጥናት ህግ ተከባሪነት እና ማህበረሰብ ተጽእኖ ግምገማ ዳይሬክተር አቶ ለሜሳ ጉደታ ቀርቧል ።
በሰነዱ የአከባቢ ጥበቃ የህግ ማዕቀፎች እንዲሁም የፕላስቲክ ብክለት ፣ የወንዝ ብክለት እና የድምፅ ብክለት ምንነት፣ ዋና ዋና መንስኤዎች፣ የሚያስከትሉት ጉዳት እና እንዴት መከላከል እንደሚገባ በዝርዝር ተጠቅሷል ።
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አዋጅ ቁጥር 1383/2017 የደረክ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ በአዲስ አበበ ፍትህ ቢሮ አቃቢ ህግ አልማዝ ክንዴ በዝርዝር ቀርቧል ።
የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ ቁጥር 1383/2017 ተፈፃሚነት የአካባቢ ብክለት በአካባቢ፣ በሰዎች ደህንነትና ጤንነት ላይ እያደረሰ ያለውንና እየተባባሰ የመጣውን ተፅዕኖ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያግዝ ነው።
የፕላስቲክ ምርቶች /ፌስታሎች / የአከባቢ ስነምህዳር ብሎም የሰዎች እና የእንስሳት የጤና ጠንቅ በመሆናቸው ህብረተሰቡ እነዚህን የጤና ጠንቅ የሆኑ ምርቶችን ባለመጠቀም አጠቃላይ የስነምህዳር ጤንነትን በማስጠበቅ ሂደት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ተገልጿል ።
በመድረኩ የአራቱ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች እና ከክፍለ ከተማ አስከ ወረዳ ያሉ የተቋማቱ ኃላፊዎች ተገኝተዋል ።
በመጨረሻም ከተሳታፊዎች ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ የቀጣይ ስራ እቅድ የቀረበ ሲሆን የአፈፃፀም አቅጣጫዎች በበላይ አመራሮች በማስቀመጥ መድረኩ ተጠናቋል፡፡
መረጃው :- የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ነው።
ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች ፦ https://linktr.ee/aacodeenforcement
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments