ባለስልጣኑ የፓራሚሊተሪ ኦፊሰሮች የሥልጠና ማጠቃለያ እና አዲስ የደንብ ልብስ ትውውቅ አደረገ
ባለስልጣኑ የፓራሚሊተሪ ኦፊሰሮች የሥልጠና ማጠቃለያ እና አዲስ የደንብ ልብስ ትውውቅ አደረገ
13/10/2018 ዓ.ም
****አዲስ አበባ****
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን የፓራሚሊተሪ ኦፊሰሮች የሥልጠና ማጠቃለያ እና የደንብ ልብስ ትውውቅ ፕሮግራም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አበቤ እንዲሁም የከተማው ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በታላቅ ድምቀት አካሂዷል ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አበቤ የከተማ አስተዳደሩ ተቋሙን ለማደራጀት የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ ቆይቷል።በዚም አግባብ ባለስልጣኑ እራሱን በአስራር፣ በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ አዘምኖ ለሌሎች ተቋማት ጭምር ተምሳሌት በመሆን ላይ ይገኛል ይህን አርአያነቱን አጠናክሮ በመቀጠል እራሱን ብራንድ ተቋም በማድረግ የከተማዋን ራዕይ እውን ለማድረግ እየሰራ ይገኛል ብለዋል ።
የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ እንደገለጹት ተቋሙ ራሱን በዕውቀት፣ በቴክኖሎጂና በሰለጠነ የሰው ኃይል ለመገንባት ሰፊ የሪፎርም ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። በዚህም በ2017 በጀት ዓመት ከከተማ አስተዳደሩ የተሰጠው እውቅና ለበለጠ ስራ መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑን አስታውሰዋል።
በ2018 በጀት ዓመት የተቋሙን አመራሮችና አባላት አቅም ለመገንባት በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ፣ በሰንዳፋና አዳይቱ ማሰልጠኛ ማዕከላት በ10 ተከታታይ ዙሮች የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠና ተሰጥቷል።
በዚህ ስልጠና ላይ 7,893 የፓራ ሚሊተሪ አባላት እና 148 አመራሮች በድምሩ 8,039 ሰልጣኞች ተሳትፈው ስልጠናቸውን በስኬት ማጠናቀቃቸው ሻለቃ ዘሪሁን ገልጸዋል።
የአቅም ግንባታ ስልጠና አባላቱ ከህዝብ ጋር በክብርና በሰላማዊ መንገድ እንዲግባቡ፣ ህግና ስርዓትን ያለ ምንም አድልዎ እንዲያስከብሩ፣ እንዲሁም የተሟላ ስነ-ምግባርና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክህሎት ኖሯቸው ህዝብን በታማኝነት እንዲያገለግሉ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተመላክቷል።
ተቋሙ እየገነባው ካለው ዘመናዊ አደረጃጀትና ሙያዊ ስነምግባር የሚመጥን አዲስ የደንብ ልብስ በዛሬው ዕለት በይፋ አስተዋውቋል።
ይህ አዲስ የደንብ ልብስ አለም አቀፍ ተሞክሮዎችንና ደረጃዎችን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ሲሆን አባላቱም ይህንን አዲስ የደንብ ልብስ ሲለብሱ ትልቅ ህዝባዊ አደራ መሸከማቸውን ተገንዝበው በኃላፊነት ስሜት መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን፣ በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ በንቃት ለመሳተፍ የ90 ቀን እቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱ ተገልጿል። በዚህም አቅመ ደካማ ወገኖች የመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የወላጆችን ማዕድ ማጋራት፣ የደም ልገሳ እና የአደጋ ስጋት ቅነሳ ተግባራት በዋናነት እንደሚከናወኑ ተጠቁሟል።
በዕለቱ በስራ ላይ እያሉ የአካልና የጤና ጉዳት የደረሰባቸው አባላትና የሰማዕታት ቤተሰቦችም በልዩ ክብር እንደሚታሰቡና የሚደረግላቸውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
ዘገባው፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው
ጠንካራ የአገልግሎት ስርዓት ያላቸው ፣ ስነምግባር የተላበሱ ፣ አገልጋይ ባለሙያዎችን እና አመራሮችን የመፍጠር ተቋማዊ የሪፎርም ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች ፦ https://linktr.ee/aacodeenforcement
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments