የመንገድ መሰረተ ልማት ደህንነትን ጥበቃና ጽዳት...

image description
- In code inforcement    0

የመንገድ መሰረተ ልማት ደህንነትን ጥበቃና ጽዳት በተመለከተ የተቀናጀ የቁጥጥር ስርዓት ሊተገበር መሆኑ ተገለጸ

የመንገድ መሰረተ ልማት ደህንነትን ጥበቃና ጽዳት በተመለከተ የተቀናጀ የቁጥጥር ስርዓት ሊተገበር መሆኑ ተገለጸ

                     ሐምሌ 23/2018 ዓ.ም
                       **አዲስ አበባ**

የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን እና የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ የክረምት ወራት በመሆኑ የመንገድ መሰረተ ልማት ደህንነት እና ጽዳት ስራዎችን በተመለከተ የሚስተዋሉ የመንገድ መሠረተ-ልማቶች ጉዳት ለመከላከል በቅንጅት መስራት የሚያስችል የውይይት መድረክ አካሄዱ።

በውይይት መድረኩ የሁለቱም ተቋማት የማእከል እና የክፍለ ከተማ ኃላፊዎች በተገኙበት ጌዜው ክረምት በመሆኑ  የከተማዋን የመንገድ መሰረተ ልማት በአንድአንድ ግዴለሽ የግንባታ ተቋማትና ግለሰቦች የሚስተዋሉ የደንብ መተላለፎች ለመከላከልና ጽዳታቸው  ማስጠበቅ በተመለከተ የሚተገበሩ አሰራሮች ላይ ውይይት ተደርጓል።

የመድረኩን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ እና የክትትል ቁጥጥርና እርምጃ አወሳሰድ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከፍያለው ታደሰ አዲስ አበባ የሀገራችንና የአፍሪካ መዲና እንዲሁም የበርካታ አለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በመሆኗ የጽዳትና የውበቷ ተግባር የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ እና ለአፍታም መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ከፍያለው አክለውም ከተማችን በቅርቡ የምታስተናግደውን የCOP 32 ጉባኤ ጨምሮ ለተለያዩ ሁነቶች  እንደሚካሄድ ጠቁመው በተለይም በግንባታ ተሽከርካሪዎች  አማካኝነት ጎማቸው ሳያጸዱ የሚወጣ ጭቃ፣ አፈርና ያልተሸፈነ የህንጻ ግንባታ ተረፈ ምርት በአስፋልት መንገዶች ላይ የሚያደርሱትን ጉዳትና ማቆሸሽ በህጉ መሠረት ስርዓት ማስያዝና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በቅኝት የተገኙት ለሚ ኩራ፣ አራዳ፣ ቂርቆስ፣ ንፋስ ስልክ፣ አቃቂ፣ ቦሌ በሌሎችም ክፍለ ከተሞች በአስፋልት መንገዶች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመግታት የተቀናጀ የቁጥጥር ስራ እንደሚሰራ ተመላክቷል።

የአዲስ አበባ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ዴሲሳ በበኩላቸው አሰራሩን ወደ ሙሉ ተግበራዊነት ከማስገባትና የትኛውም አይነት አስተዳደራዊ ቅጣት ከመጣሉ በፊት ህብረተሰቡና የሚመለከታቸው አካላት በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ግንዛቤ የመፍጠር ስራው ከተከናወነ በኋላ ደንብ በሚተላለፉ አካላት ላይ የማስተካከያና የደንብ ማስከበር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ ተቋማት እና ግለሰቦች ከእኩይ ተግባራት እንዲታቀቡ  መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዘገባው :- የባለስልጣኑ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው።


Comments

Nothing was found.

Leave Your Comments