የአደጋ ስጋት ደህንነት ደንብ ቁጥር 132/201...

image description
- In code inforcement    0

የአደጋ ስጋት ደህንነት ደንብ ቁጥር 132/2014 እና መመሪያ ቁጥር 163/2017 ወደ ሙሉ ትግበራ ሊገባ መሆነ ተገለፀ

የአደጋ ስጋት ደህንነት ደንብ ቁጥር 132/2014 እና መመሪያ ቁጥር 163/2017 ወደ ሙሉ ትግበራ ሊገባ መሆነ ተገለፀ

            ነሐሴ 01/2018ዓ.ም
               ** አዲስ አበባ** 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን ደንብ ቁጥር 132/2014 እና መመሪያ ቁጥር 163/2017 ያወጣው በከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የህንፃዎች ከፍታ፣ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋትና የህዝብ ቁጥር እድገት ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከልና የህይወትና ንብረት ደህንነትን ለማረጋገጥ መሆኑ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ደንብና መመሪያው ላይ ለህብረተሰቡ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በቀጣይ ተጠናክረው የሚሰሩ መሆኑን ገልጸው፣  ደንቡን ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ተናግረዋል።

​የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ኮማንደር አህመድ መሐመድ በመግለጫቸው እንደተናገሩት የአደጋ ስጋት ደህንነት ደንብ ቁጥር 132/2014 እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአደጋ መከላከል ፣ ቁጥጥር ፣ ፍተሽና ብቃት ማረጋገጥ ሥርዓት መመሪያ ቁጥር 163/2017  የከተማችንን ህብረተሰብ ህይወትና ንብረት ከአደጋ ስጋት ለመጠበቅ የወጣ ደንብና መመሪያ ነው።

የደንቡ ዋና ዓላማ በከተማዋ ውስጥ አደጋ እንዳይደርስ አስቀድሞ መከላከል እንደሆነ ገልጸው፣ ከዚህ ቀደም አደጋ ከደረሰ በኋላ ይደረግ የነበረውን የመከላከል ተግባር ሙሉ በሙሉ አስቀድሞ ወደ መከላከል ያሸጋገረ አሰራር መሆኑን አብራርተዋል።

ኮማንደር አህመድ አያይዘውም መመሪያው ተፈጻሚ የሚሆነው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ መሆኑን በመጠቆም፣ ተቋሙ በከተማዋ የሚገኙ ተቋማትን የሙያና የቴክኒክ ድጋፍ ከመስጠት ባለፈ የፍተሻና ቁጥጥር ስራ በማካሄድ የብቃት ማረጋገጫ (ሰርቲፋይድ) የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

በደንቡ መሠረት ማንኛውም የህዝብ መገልገያ ህንፃ፣ የንግድ ተቋም ወይም አደገኛ ንጥረ ነገሮችን የሚያከማች ድርጅት በየዓመቱ ከአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ ደህንነት ብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት የመያዝ እና የማደስ ግዴታ ተጥሎበታል።

ተቋማትና የህንፃ ባለቤቶች ደረጃውን የጠበቀ የውሃ መቅጃ ሀይድራንት (Hydrant)፣ የእሳት ማጥፊያ ሲሊንደሮች፣ የጭስ ማወቂያዎችና የስፕሪንክለር ስርዓት የመገጠም እንዲሁም በህንፃ ዲዛይኖቻቸው ውስጥ የአደጋ ጊዜ ማምለጫ መንገዶችን የማካተት ግዴታ አለባቸው።

የተጣሉ የደህንነት መስፈርቶችን ሳያሟሉ በሚገኙና ህጉን በሚጥሱ አካላት ላይ እንደ ጥፋቱ ደረጃ ከብር 10,000.00 እስከ ብር 100,000.00 የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት የሚጣል ሲሆን፣ በተጨማሪም የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ በመስጠት በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያላስተካከሉ ተቋማት የንግድና ስራ ፈቃዳቸው እንዲታገድ ወይም እንዲሰረዝ የሚደረግ ይሆናል።

ዘገበው ፡-የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳሬክቶሬት ነው፡፡


Comments

Nothing was found.

Leave Your Comments